You are currently viewing International Biodiversity Day celebrated at regional level in Ethiopia

ዓለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ቀን በዓል በክልል ደረጃ ተከበረ

ዳኤ ቡሹ!!! “እንኳን የእምቅ ብዝሀ ሕይወት ሀብት ባለቤት ወደሆነችው ሲዳማ ክልል በሰላም መጣችሁ” በሲዳማ ብ/ክ/መ አካባቢ፣ የሲዳማ ብ/ክ/መ አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩትና ፔለም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በብዝሀ ሕይወት ና የስርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሄደ።

መድረኩ አለም አቀፉን የብዝሀ ህይወት ቀን በሲዳማ ክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማክበር ያለመ መሆኑን አቶ ሽታዬ ዩሙራ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ለይ ተናግረዋል።

እንሰትና ሌሎች የስራስር ተክሎች አገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚጫወቱት ሚና ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት የገለፁት አቶ ሽታዬ የክልሉን የብዝሀ ሕይወት ሀብት፣ ነባር የማህበረሰብ እውቀትና ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቅርስ ለመጠበቅና ለማጥናት ባለድርሻ አካላት ግንባር ቀደም ሚናን እንዲወስዱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ ስለብዝሀ ሕይወት ፅሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ፈለቀ ወ/የስ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር የዛሬ 30 አመት በካናዳ በጥቂቶች የተፈረመው አለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ስምምነት አላማውን የተቀበሉት በዝተው አሁን ላይ በሲዳማ ክልል ወረዳዎች ድረስ መዋቅሩ ሰፍቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን፣ ያልተገደበ የህዝብ እና የኢኮኖሚ እድገት በአካባቢና በብዝሀ ሕይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳርፍ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“አርሶ አደሩ በተግባር የተፈተነ በልምድ የዳበረ እውቀት ባለቤት ነው። አርሶ አደሩን መስማት የተመራማሪውን የግንዛቤ አድማስ ያሰፋል። ምርምሩንም በጠንካራ መሰረት ላይ ይጥላል” ያሉት ዶ/ር ሀይሉ አርአያ ፔለም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

በመጨረሻም 21ኛው አለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ቀን "ለሁሉም የጋራ የወደፊት ሕይወት መገንባት" በሚል መሪ ቃል ዛሬ የሲዳማ ክልል መዲና በሆነችው ሀዋሳ ከተማ መከበር መጀመሩን የገለፁት የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንሰቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዮ የበአሉ መከበር አላማ በብዝሀ ሕይወት ላይ እየደረሱ ያሉ ስጋቶችን ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር በጥበቃ እና ዘለቄታዊ አጠቃቀም በማስፈን ሒደት ውስጥ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ለማስቻል መሆኑን ተናግረገዋል።