በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በወቅታዊ ሀገራዊ ሰነድ ዙሪያ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከሰራተኞቹ ጋር ውይይት ተደረገ፡፡
“የመጋቢታውያን የለውጥ ፍሬዎችን እና የነገ ተስፋዎች” የተሰኘ ሀገራዊ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የተቋማት ሪፎርም እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን ያካተተ የመወያያ ሰነድ በወ/ሮ እጥፍወርቅ ዘውዱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ከሰራተኞችም ሰነዱን የተመለከቱ ገንቢ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን ጥያቄዎችም ቀርበው በሚመለከታቸው አካላት ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ ዶ/ት አብዮት ብርሃኑ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሾች የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
አሰራሮችን ማዘመን፣ የምርምር ውጤቶችን ተደራሽ ማድረግ፣ የተጀመሩ ድንቅ ተግባራትን ማስቀጠል፣ የአረንጓዴ አሻራ የቅድመ-ዝግጅት ተግባራትን ማጠናከር፣ የተቋሙን ምድረ-ግቢ ለተገልጋዮች ምቹ ማድረግ፣ የክፍያ መመሪያን ተግባራዊ ማድረግ እና ፕሮጀክቶችን በማምጣት ሰራተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡
ዶ/ር ካርታ ካስኬ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው በቁጭት በመስራት ኢትዮጵያን በጋራ እናሻግራለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሁላችንም ወደ ራሳችን ልንመለከት ይገባል ካሉ በኋላ እያንዳንዱ ሰራተኛ ለሀገራዊ ለውጡ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
