ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ካርታ ካስኬ እና ዶ/ር አብዮት ብርሃኑ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከተቋሙ የማኔጅመንት አካላት ፣ ተመራማሪዎች፣ የጊኒር ወረዳ ከተማ አስተዳደርና የአካባቢው ህብረተሰብ የምርምር ሥራ ተሳታፊ ገበሬዎች በሃረዋ አንድ መስክ ጂን ባንክ ጉብኝት ምልከታ ለማድረግ በሥፍራው ተገኝተዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ በሃገር ባህል ወግና ሥርዓት በአባቶች ፤ በእናቶች የባህላዊ ምግብ ዝግጅት ለእንግዶች በማዘጋጀት አቀባበል አድርገዋል።
በዕለቱ አቶ ውብሸት ተሾመ የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ብዝሃ ህይወት ምርምር መሪ ሥራ አስፈፃሚ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በሃረዋ ቀበሌ ዜሮ አንድ ያሉትን ተመራማሪ አርሶአደሮች እና እዚህ ለደረሱበት ጥረት ስፖንሰር ያደረጉትን ፕሮጀክቶችንና አስተዋፅዖ ያደረጉትን ሁሉ መሪ የተቋሙ ተመራማሪዎችን በአካልም ዛሬ ያሉትን ዶ/ር የሺጥላን አመስግነውና የጉብኝቱን ዓላማ ገልፀው የብዝሃ ህይወት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ካርታ ካስኬ የመክፈቻ ንግግርና የወደፊት አቅጣጫ እንዲሰጡ ጋብዘዋል።
ዶ/ር ካርታ ካስኬ ለአርሶአደሮች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የወረዳ አስተዳዳሪ እንዲሁም ለቀበሌው ሃላፊዎች ሰላምታ አቅርበው ኢትዮጵያ የብዝሀ ህይወት ሃብት የታደለች ናት ሲሉ ንግግራቸውን ጀምረዋል።
የብዝሀ ህይወት ሃብቷ ጥቅም ላይ እንዲውል በዚህ ዓይነት ወደ አርሶ አደሩና ወደ ተጠቃሚው እየተፈተሸ እናንተ ይሆነናል ያላችሁትን ፤ የቀደሙት የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ያቆዩልንን ዘረመል በኢትዮጵያ የዘር ባንክ ውስጥ ከተቀመጡት16ሺ የስንዴ ዓይነቴዎች 80ዎቹን አውጥቶ በመፈተሽ 4ቱን እንደዚህ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት በማድረጋችሁ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ።
ገና ተጀመረ እንጂ ከስንዴ ውጪ የገብስ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ፣ የማሽላ፣ምስር ፣ ኑግ … ገና ብዙ ያልተነካ አለ፤ በዚህ ከቀጠልን የኢትዮጵያን ሃብት ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ማመቻቸት ይቻላል።
ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባችሁ ግን የወሰዳችሁት ዝርያ ውጤት በሌሎች ገበያ ላይ እንዳይውል ተመዝግቦ መሰብሰብ ይኖርበታል፤ ብለዋል።
ይህን ለማድረግ የኛ ተመራማሪዎች እነ ዶ/ር የሺጥላና እነ ዶ/ር ታመነ ይህንን በቀጣይነት የሚሰሩ ነው የሚሆነው፤ ካሉ በኋላ ገና ሳናይ ብዙ ማለት አይገባኝም እዚህ በመገኘቴ የተሰማኝን ደስታ ልገልፅላችሁ አወዳለሁ ፣ አመሰግናለሁ ።
በዶክተር የሺጥላና ፣ በአቶ ውብሸት ልዑኩ ወደ ጉብኝቱ እየተመራ በሽታን የሚቋቋም፣ ድርቅን የሚቋቋም፣ ጥሩ ምርትና ጣዕም ያላቸውን ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ አራቱንም የስንዴ ዓይነቴ በማሳ ላይ በተቋሙ ተመራማሪ ባለሙያዎችና ሁለት ታታሪ የገበሬ የተግባር ተመራማሪዎች የመስክ ጉብኝቱ ጀንበር በማዘቅዘቋ ተገደበ እንጂ ሙያዊ ትንትኔና ውይይቱ ከራስ ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር መግባባትና የእርቅ ድርድር የጀመርንበት እየመሰለ ፣ ተስፋ ያዘለ ነበር።
ይህ ግኝትና ውጤት መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት በአዲስ ራዕይ ተስፋ ሰንቆ የሚነሳበት ፣ የሚያንሰራራበት ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ብልፅግና የሚተጋበት፣ ከተሳታፊ ብሩህ ገፅ ይታይ አየሩም መዐዛው ያውድ ይናገር ነበር።
