የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በSeeds for Resilience Project ድጋፍ በጊኒር ወረዳ ሐረዋ 1 ቀበሌ በሚገኘው የማሕበረሰብ ዘር ባንክ ውስጥ ላለፉት ሦስት ዓመታት ባካሄደው አርሶ አደርን ያሳተፈ የነባር ስንዴ ምርምር አካባቢውን የተላመዱ፣ ምርታማ እና በሽታ በመቋቋም ችሎታቸው ተመርጠው ዘራቸው የተባዙ አራት የነባር ስንዴ ዓይነቴዎች ቁጥራቸው ከ45 በላይ ለሚሆኑ የጊኒር ማህበራዊ ዘር ባንክ አባላት ለእያንዳንዳቸው አንድ መቶ ኪሎ ግራም ዘር ተሰራጭቷል፡፡
በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የአዝርዕትና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ውብሸት ተሾመ የዘር ሥርጭቱ ለማህበሩ አባላት የማሰራጨቱን አስፈላጊነት ገልጸው እያንዳንዱ ዘር የሚወስድ የማህበሩ አባል ዘሩን በአግባቡ መዝራትና የእንክብካቤ ስራዎችን ወቅቱን ጠብቆ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በማከልም የዘር ስርጭቱን ለማከናወን እንዲቻል ቀደም ሲል ከማህበሩ ዘር ወስደው ያልመለሱ አባላት በቅድሚያ ዘሩን መመለስ እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የማህበሩ አባላት ያለባቸውን ዕዳ ለመክፈል ስምምነት ላይ ተደርሶ ሁሉም አባላት ክፍያቸውን ፈጽመው የዘር ስርጭት እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡
ዶ/ር የሺጥላ መክብብ በበኩላቸው የስንዴ ዓይነቴዎቹን በመምረጥ ሂደት የተመራማሪዎች እና የአርሶ አደሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ የተመረጡት የስንዴ ዓይነቴዎች አካባቢውን የተላመዱ፣ ምርታማ እና የስንዴ በሽታ (rust disease) የመቋቋም አቅም ስላላቸው የአርሶ አደሩን የዘር አቅርቦትና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡ የአርሶ አደሩ የዘር ጥያቄ ከፍተኛ ቢሆንም የዘር ሥርጭቱን ለወንድ እና ሴት አርሶ አደሮች ማዳረስ ተገቢ በመሆኑ ዘሩ በፍትሀዊነት እንዲሰራጭ የተደረገ ሲሆን፣ በቀጣይነት ዘር የወሰዱ አርሶ አደሮች ማሳ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የተመረጡትን የስንዴ አይነቴዎች (farmers varieties) በቀጣይነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የማስመዝገብ ሥራ እንደሚሠራና ዘሩ ተመሳሳይ የግብርና ስነ-ምህዳር ወደ አላቸው አከባቢዎች የማስፋት ሥራ እና የገበያ ትስስር እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ በጊኒር ማህበራዊ ዘር ባንክ ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ነባር የስንዴ ዓይነቴዎችን ለማግኘት በምርምር ጣቢያው ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ አርሶ አደርን ያሳተፈ የምርምር ሥራ በSeeds for Resilience Project ድጋፍ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች፣ የጎባ ብዝሀ ሕይወት ማዕከል ተመራማሪዎች፣ የጊኒር ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ባለሙያ እንዲሁም አርሶ አደሮች አማካኝነት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
