You are currently viewing The Seventh Annual Ethiopian Biosphere Reserve Network Forum Held

ሰባተኛው ዓመታዊ የኢትዮጵያ ባዮስፌሮች ሪዘርቭ ኔትወርክ መድረክ ተካሄደ

ሰባተኛው ዓመታዊ የኢትዮጵያ ባዮስፌሮች ሪዘርቭ ኔትወርክ መድረክ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በጂማ ከተማ ተካሄደ፡፡

የጂማ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አስራት እሸቱ ባስተላለፉት መልዕክት ተቀራርቦ መስራት ከሁላችንም ይጠበቃል ካሉ በኋላ በባዮስፌሮች ዙሪያ ተቀናጅተን ለመስራት ቢሯችን ክፍት ነው ብለዋል፡፡

በዩኔስኮ የአዲስ አበባ ቢሮ ኃላፊ Mr. Hambani Masheleni በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ በርካታ የማህበረሰብ ዕውቀቶች መኖራቸውን አስታውሰው ዩኔስኮ ለብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የበኩሉን ዕውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር አብዮት ብርሃኑ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ባዮስፌር ክምችቶች ብዙዎቹ ልዩ መሆናቸውን አስታውሰው የአካባቢ ማህበረሰቦችን በትምህርት፣ በዘላቂ መተዳደሪያ እና በኢኮ ቱሪዝም በማበረታታት የብዝሀ ህይወት ጠባቂዎችን ወደ አጋርነት እንቀይራለን ብለዋል፡፡

አያይዘውም በምርምር እና ቴክኖሎጂ ስነ-ምህዳሮችን መከታተል፣ የተራቆቱ መሬቶችን ወደ ነበሩበት መመለስ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ልምዶችን ማዳበር፣ የኢትዮጵያ ባህላዊ እውቀትን ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማጣመር ለዘላቂ ኑሮ ሞዴል መፍጠርም እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በበኩላቸው የባዮስፌር ሪዘርቭ ከምስረታው እስከ ስኬቶቹ ተግዳሮቶቹና ስኬቶችን የዳሰሰ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ አቶ አበራ ስዩም የደንና ግጦሽ መሬት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ የኢትዮጵያ ባዮስፌር ሪዘርቭ ኔትወርክ የአፈጻጸም ሪፖርትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የካፋ የባዮስፌር ሪዘርቭ፣ የሸካ የባዮስፌር ሪዘርቭ፣ የያዮ የባዮስፌር ሪዘርቭ፣ የጣና የባዮስፌር ሪዘርቭ እንዲሁም የመልካ ኢትዮጵያ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ውይይቱን ዶ/ር አብዮት ብርሃኑ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር የመሩት ሲሆን ለቀረቡ ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ ዶ/ር ግርማ እሸቱ የ2025 የድርጊት መርሀ-ግብር አቅርበው የጸደቀ ሲሆን የተጓደሉ የኔትዎርክ አባላትን በማሟላት መድረኩ ተጠናቋል፡፡