የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት “Restoration and Conservation of Threatened and Endemic Fabaceae Species in Ethiopia” በሚልርዕሰ-ጉዳይዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋርየፕሮጀክት ማስጀመሪያ ወርክሾፕ ሚያዝያ 04 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄደ፡፡
ዶ/ር አብዮት ብርሃኑ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዶ/ር ካርታ ካስኬ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዝሀ ሕይወት ኃብቷ የታወቀች መሆኗን አስታውሰው ለሳይንሳዊ ግኝቶች ወሳኝ የሆኑ የበርካታ የዕፅዋት ዝርያዎች መኖሪያ መሆኗን አክለዋል። ይሁን እንጂ ሰው ሰራሽና እና ተፈጥሯዊ ግፊቶች በእነዚህ ዝርያዎች ላይ አደጋ ቢደቅኑም ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ (CRGE) ስትራቴጂ እና አረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብርን በመተግበር በርካታ እርምጃዎችን ወስዳለች ብለዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የብዝሀ ሕይወት ስምምነት ፈራሚ ሀገር እንደመሆኗ ብዝሀ ሕይወትን በመጠበቅ ከኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂዎች ጋር ለማቀናጀት በመስራት ላይ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአካባቢ ጥበቃ፣ የመልሶ ማልማት ስራዎች፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ አቅርቦት እና መሰል ጉዳዮች ለሴቶች፣ዝቅተኛ ገቢ ለላቸው የኅ/ሰብ ክፍሎች፣ ለስራ አጥ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች አማራጭ የመተዳደሪያ መስክ እንደሚሆን አክለዋል፡፡ በዚህም ዘላቂ አሰራሮችን መተግባር፣ በብዝሀ ህይወት ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቀነስ ፕሮጀክቱን በስኬታማነት ለማጠናቀቅ ሁሉም ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ሙሉ ድጋፍና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም Franklinia Foundation ላደረገው ከፍተኛ የገንዘብ አስተዋፅዖ ከልብ አመስግነዋል።
የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ፣ ዓላማዎች፣ አበይት ጉዳዮችን እና ውጤቱን ጨምሮ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ሳምሶን ሽመልስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሀረር ብዝሀ ሕይወት ማዕከል፣ የባህርዳር ብዝሀ ሕይወት ማዕከል እና ከምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የተውጣጡ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ስለ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ገለጻ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ፕሮፌሰር ዘመዴ አስፋው እና ዶ/ር ሙሉጌታ ከበደ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቱ በማንበር፣በግንዛቤ ፈጠራ እና በኑሮ ሁኔታ ላይ ያለውን አቅም በማሳየት ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማርዮ እና ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ሥነ-ምህዳሮችን ወደ ነበሩበት መመለስ፣ ልዩ የሆኑ ዝርያዎችን ማንበር እና በብዝሀ ሕይወት የበለፀገች ሀገር የመገንባት አስፈላጊነትን ጠቁመዋል፡፡ ያሉትን እድሎች በመጠቀም ጠንካራ ትስስር መፍጠርና ተግባራዊ ማድረግ ለብዝሃ ህይወት ሀብቶች ማንበር ያለውን አስተዋፅኦም አስታውሰዋል፡፡
ተመሳሳይ አስተያየቶች በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች እና ሥራ አስፈፃሚዎች ዶ/ር ምስክር ተሰማ፣ ዶ/ር ደመቀ ዳቲኮ፣ ዶ/ር ተስፉ ፈከንሳ፣ አቶ ግሩም ፋሪስ እና ወይዘሮ እጥፍወርቅ ዘውዱ የተሰጡ ሲሆን ሁሉም ተሳታፊዎች የፕሮጀክቱን አተገባበር ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። በመድረኩ ላይ በFranklinia Foundation የተደገፈው ፕሮጀክት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በማጎልበት፣ በማህበረሰቡ እና በጥብቅ ስፍራዎች ላይ ለውጥ ለማምጣት የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ ሀሳቦች ቀርበውበታል፡፡
ተሳታፊዎች ላቀረቧቸው ጥያቄዎችን ተገቢ ምላሾች ሲሰጡ የቀረቡ አስተያየቶች በግብዓትነት እንደሚወሰዱ የፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ሳምሶን ሽመልስ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ካርታ ካስኬ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ለፕሮጀክቶች ስኬታማነት ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስታውሰው ለFranklinia Foundation የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም የስልጠና ፣የማማከር ፣የፕሮጀክት ድጋፍ እና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ ፕሮጀክቱን ቀርፆ ለዚህ ደረጃ ላደረሱት አካላት ጥረት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
