የኢትዮጵያ የማይክሮባዮሎጂ ማህበር 4ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ከግንቦት 17-18 ቀን 2011 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።
ኮንፈረንሱ ”የደቂቅ አካላት ቴክኖሎጂ እና የምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ያተኮረ ሲሆን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂን አስፈላጊነትን ያሳያል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ከተማ ባጫ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በደቂቅ አካላት ላይ የሚካሄድ ምርምር ዘላቂነት ያለው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ደቂቅ አካላት የአፈርን ለምነት መጨመር እንዲሁም ቆሻሻን በማስወገድ ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳሉ ብለዋል። አያይዘውም ማህበሩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ወደ መድረክ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ነው ጠቁመው የማህበሩ አባላት ግኝቶችን ወደ ማህበረሰቡ ማድረስ እንዳለባቸው አስታውሰዋል፡፡
የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ገነነ ተፈራ በበኩላቸው ደቂቅ አካላት እንደ ሌሎች የብዝሀ ሕይወት ሀብቶች እኩል ጠቀሜታ ቢኖራቸውም በቴክኖሎጂ ፈጠራ ውስጥ ክፍተት አለ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አማካይነት የተደረገው ምርምር የአፈር ለምነትን ፣ የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል እና የተክሎች እድገትን ለማፋጠን አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን የተለያዩ ደቂቅ አካላትን ለይቶ ማወቅ መቻሉን ጠቅሰዋል።
እነዚህን የምርምር ግኝቶች ለማህበረሰቡ በማዳረስ ውጤታማ ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅም ማዳበር ተገቢውን ትኩረት ይጠይቃል ብለዋል ዶክተር ገነነ።
ፕሮፌሰር ፈቃዱ ረጋሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ኮሌጅን በመወከል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የባዮቴክኖሎጂን ጉዳይ የሚመለከት በመሆኑ የባዮቴክኖሎጂ ቴክኖሎጂን ትክክለኛ አያያዝ ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉባኤው ላይ የጥናት ወረቀቶች ቀርበው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውውይት ተደርጎባቸዋል።
የኢትዮጵያ የማይክሮባዮሎጂ ማኅበር እ.ኤ.አ. በ 2014 የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡
on The Use of Microbial Technology Plays An Important Role In The Attainment of Food Security.