የማህበረሰብ ዘር ባንክ አዝርዕቶችንና አትክልቶችን ለመጠበቅ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ ሲሆን በ 1970 ዎቹ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ የሰብል ደህንነትን ለማረጋገጥ የተቋቋመ ነው ተብሏል።
አዲሱ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የአዝርዕቶችንና ሆርቲካልቸር ብዝሃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት በዓለም ምግብና ግብርና ድርጅት ድጋፍ እየተተገበረ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ውስጥ መደበኛ ባልሆነ መልኩ ዘሮችን ለመጠበቅ ብሔራዊ የማህበረሰብ የዘር ባንክ ተብሎ ተሰይሟል።
የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማሪዮ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በተቋሙ ስር 30 የሚሆኑ የማህበረሰብ ዘር ባንኮች ያሉ ሲሆን ነባር ሰብሎችን በአርሶ አደሩ እጅ ማቆየት ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ታመነ ዮሐንስ (ዶ/ር) የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የፕሮጀክቱ ዓላማም የማህበረሰብ ዘር ባንኮችን ሥራ መደገፍ ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከርና እና የልምድ ልውውጥ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም የጠፉ ሰብሎችን በማጥናት መተካት፣ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ አርሶ አደሩን የበለጠ አምራች ማድረግ ከተከናወኑት ተግባራት አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በመጨረሻም ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና ገንቢ አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቷል።