You are currently viewing Participatory Wheat Farmers’ varieties selection for climate resilience, seed handover programme held at Chefe Donsa Community Seed Bank

የተመረጡ ዘሮችን ለአርሶ አደሮች የማስረከብ መርሀ-ግብር ተከናወነ

አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የነባር ስንዴ ዝርያዎች መረጣና የማስረከብ መርሀ-ግብር በጨፌ ዶንሳ ማህበራዊ ዘር ባንክ መጋቢት 03 ቀን 2017 ዓ.ም ተከናወነ፡፡

ዶ/ር መለሰ ማርዮ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የአርሶ አደሩና የሳይንሱን ዕውቀት በመጠቀም የአየር ንብረት ተጽዕኖን መቋቋም የሚችሉ የነባር ዘሮችን ማግኘት እንደሚቻል አስታውሰው የተመረጡ ዘሮችን ለሌሎች አርሶ አደሮች ማስተላለፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ስለ PR-191 ፕሮጀክት አጠቃላይ መረጃ በዶ/ር ታመነ ዮሀንስ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የቀረበ ሲሆን የነባር ዘሮችን ጠቀሜታ ተናግረው ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ተግባራትን ዘርዝረዋል፡፡

አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የነባር ዘር ማሻሻያ ሂደትና የተከናወኑ የምርምር ስራዎችን ዶ/ር ባሳዝን ፋንታሁን ያቀረቡ ሲሆን አርሶ አደሮችም በስንዴ ነባር ዘር መረጣ ሂደት የነበራቸውን ተሞክሮ አብራርተዋል፡፡

አቶ ከበደ ሸዬ የጨፌ ዶንሳ ማህበራዊ ዘር ባንክ ሊቀመንበር ስለ ጥቁር ስንዴ ተፈላጊነትና ያለበት ደረጃ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የወረዳውና የቀበሌው አመራሮችና ባለሙያዎችም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ውብሸት ተሾመ በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የአዝርዕትና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው የምርምር ስራው እየሰፋ ሊሄድ እንደሚገባው አስታውሰው እንደ ልጆቻችሁ ተንከባክባችሁ ያባዛችሁትን ነባር ዘሮች ለአካባቢው ማህበረሰብ የማሰራጨት ተግባራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

የተመረጡ ዘሮችን ለአርሶ አደሮች የማስረከብ መርሀ-ግብር ተከናውኖ ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር የማጠቃለያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ዶ/ር ፈለቀ በመልዕክታቸው ምርምርና የማህበረሰብ ዕውቀትን ያጣመረ የምርምር ስራ በመከናወኑ መደሰታቸውን ተናግረው በቀጣይም ተሞክችሁን ለሌሎች የምታስተላልፉበትን መንገድም እንፈጥራለን ብለዋል፡፡