You are currently viewing The Institute is working to focus on distributing and disseminating valuable information on wild and in-water animals, which are known to be unique to the country.

ኢንስቲትዩቱ ለሀገሪቱ ልዩ እንደሆኑ በሚታወቁ የዱር እና በውሃ ውስጥ እንስሳት ላይ ጠቃሚ መረጃን በማሰራጨት ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው

ከሕዝብ ክንፍ፣ ባለድርሻ አካላትና ተመራማሪዎች ጋር በዱር እና በውሃ ውስጥ እንስሳት ጥበቃ እና ዘላቂ አጠቃቀም ላይ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በቢሾፍቱ የምክክር መድረክ በተካሄደበት ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማሪዮ እንደተናገሩት የዱር እና የውሃ ሀብቶች ከስነ -ምህዳሮቻቸው ዋጋ ባሻገር ለተለያዩ አገልግሎቶች አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በምግብምንጭነት፣ በቱሪዝም ፣ በመድኃኒቶች ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በውጭ ምንዛሪ ውስጥ ያላቸው አስፈላጊነት የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም የብዝሀ ሕይወት ሀብቶቹ ላይ አደጋ ስለተደቀነ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የብዝሃ ሕይወት ሀብቶቹን በአግባቡ መጠበቅና እና መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

የእንስሳት ብዝሃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አሰፋ በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ በቤት እንስሳት፣ በዱር እንስሳትና በውሃ ውስጥ የብዝ ሕይወት ሀብቶች ላይ የማንበር፣ የምርምርና በዘላቂ አጠቃቀም ላይ እየሠራ መሆኑን ተናግረው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 15 ጥናቶች የተካሄዱ ሲሆን 5 የምርምር ወረቀቶች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ለወደፊቱ ሥነ -ምህዳራዊ እና የጄኔቲክ ሀብት ጠቀሜታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሀገሪቱ ብርቅዬ ተብለው በሚታወቁት የዱር እንስሳት እና የውሃ ውስጥ እንስሳት ላይ በማተኮር የጥናትና ምርምር ስራ ይካሄዳል ብለዋል አቶ አብርሃም።

በእነዚህ ጥናቶች መሠረት የእንስሳት ብዝሃ ሕይወትን በዘላቂነት ጥቅም ላይ በማዋል በዘርፉ አዎንታዊ ውጤት ማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

በሀዋሳ ብዝሃ ሕይወት ማዕከል ተመራማሪ ዶ/ር ደመቀ ዳቲኮ በበኩላቸው በዱር እንስሳትና የውኃ ውስጥ እንስሳት ክትትልና ጥበቃ ማድረግ ለዘላቂ ልማት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ተገቢ የክትትል ዕቅዶችን በመዘርጋት በሀብቱ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል ዶክተር ደመቀ።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ለመስራት ሀሳባቸውን አቅርበው በሀብት ንብረት ካታሎግ አስፈላጊነት ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በመድረኩ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች ቀርበዋል።

በኢትዮጵያ ከ 6875 በላይ የእንስሳት ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 191 ብርቅዬ ናቸው።