You are currently viewing A workshop titled “Mainstreaming Biodiversity in the Agricultural System of Ethiopia” was held on July 8, 2025 at Skylight Hotel

"በኢትዮጵያ የግብርና ሥርዓት ውስጥ የብዝሀ ሕይወትን ጉዳይ ማስረፅ" "Mainstreaming Biodiversity in the Agricultural System of Ethiopia." በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ሀምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡

አቶ አብደታ ሮቢ የIUCN ኢትዮጵያ ተጠሪና የBIODEV 2030 አስተባባሪ የአውደ-ጥናቱን ዓላማ ጠቅሰው የሚጠበቁ ውጤቶችንም አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ካርታ ካስኬ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የአገራችንን የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ መከተል ካለብን መንገዶች አንዱ የራሳችንን የብዝሀ ሕይወት ሀብት መንከባከብና በዘላቂነት አግባብ ስራ ላይ ማዋል መሆኑን ጠቁመው የብዝሀ ሕይወት ሀብታችን የግብርና ምርታማነት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን ለማልማት መሰረት ነው ብለዋል፡፡

 አያይዘውም ይህ ወቅት ስለ ብዝሀ ሕይወት ሀብታችን እንክብካቤ ለመነጋገርና ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ምቹ ሁኔታዎች ያሉበትና ዘርፉም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ትኩረት ያገኘበት ጊዜ በመሆኑ እድለኞች ያደርገናል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ግርማ አመንቴ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ባስተላለፉት የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያ በብዝሀ ህይወት ከበለጸጉ 25 ሜጋ ባዮ ዳይቨርስቲ ሀገራት መካከል አንዷ ሆና በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቷን ገልጸው የእፅዋት ዘር መነሻ እና ብዝሃነት ማዕከል (center of origin and diversity for crop plants) እና ከአለም 36 የአለም የብዝሀ ህይወት ሆትስፖቶች የሁለቱ የምስራቅ አፍሮሞንታን እና የአፍሪካ ቀንድ (Eastern Afromontane and the Horn of Africa) መገኛ ነች ብለዋል፡፡

 አያዘውም የአየር ንብረት ለውጥን እና የብዝሀ ህይወት መመናመንን መግታት እና በተመሳሳይ ጊዜ የማህበረሰቡን ኑሮን ማሻሻል እርስ በርስ የተያያዙ ግቦች መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ አውደ-ጥናቱ የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ዋና አጀንዳ ሆኖ የተቀናጀ ልማትን የሚያበረታቱ እድሎችን ለመፍጠር ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ገልጸው መድረኩን ላዘጋጁ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ቢቂላ ወርቅነህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን "Mainstreaming Biodiversity in the Agricultural System of Ethiopia, in the context of sustainable production" ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ውይይቱን ዶ/ር ግርማ አመንቴ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር እና ዶ/ር ካርታ ካስኬ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የመሩት ሲሆን ለቀረቡ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም ቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠው መድረኩ ተጠናቋል፡፡