በጀነቲክ ሀብቶች ጥቅም ተጋሪነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የዕጽዋት አጸድ ጠባቂዎችና ኢ-ዘቦታ ሰብሳቢዎች ጋር የምክክር መድረክ ከሐምሌ18- 19 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሄደ
በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱን የጄኔቲክ ሀብቶችን ለመጠበቅ እየሰራ መሆኑን ተናግረው ይህንን ከማጠናከር አኳያ በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም ኢትዮጵያ የጄኔቲክ ሀብቶችን ተደራሽ ለማድረግና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሕግ አውጥታለች ብለዋል።
ይህንን ደንብ በሥራ ላይ ለማዋል የጄኔቲክ ሀብቶችን ተደራሽነት እና ጥቅምን ተጋሪነትን ለመተግበር አመቺ ሁኔታ መኖር አለበት ብለዋል።
በተጨማሪም የጄኔቲክ ሀብቶች ለምርምር እና ልማት መሠረት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የጄነቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አየነው በበኩላቸው የአገሪቱ ብዝሀ ሕይወትና ተያያዥ የማህበረሰብ ዕውቀቶች በአግባቡ ተጠብቀው በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፣ ማኅበረሰቡም በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ የጀኔቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦትን እና የማህበረሰብ መብቶች ለመወሰን አዋጅ ቁጥር 482/2006) እና ደንብ ቁጥር 169/2009) አውጥታለች ብለዋል አቶ አሸናፊ።
አያይዘውም ኢትዮጵያ የናጎያ ፕሮቶኮልን በመቀበል የጀነቲክ ሀብቶችና ጥቅም ተጋሪነት የሥነ ምግባር ደንብን አዘጋጅታለች ብለዋል።
የዳርዊን ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት መሪ ሱዛን ሻሮክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወትን በማንበር ባደረገችው ጥረት የታወቀች ሀገር ናት ብለዋል። በተጨማሪም በጄኔቲክ ሀብቶች ዙሪያ የሕግ ማዕቀፎችን የማጠናከሩን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል።
ይኸው የምክክር አውደ ጥናትም ከተመራማሪዎች ጋር ከሀምሌ 27-28 ቀን 2010 ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፋዊ የብዝሀ ሕይወት ኮንፈረንስ (ሲቢዲ) የሚወክል ተቋም ነው።