You are currently viewing Ethiopian Biodiversity Institute provides awareness raising training to its staff

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ለሰራተኞቹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ

ከጥር 23-26/2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ጎልድ ማርክ ሆቴል ለኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች በተለያዩ እርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።

መድረኩን የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማሪዮ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክት በማስተላለፍ የስልጠናውን አስፈላጊነት እና አላማ ለሰልጣኞች በማስገንዘብ ከፍተውታል።

የስልጠናው በመጀመርያው ምእራፍ የመንግስት ግዥ አፈጻጸም፣ የመንግስት ንብረት አስተዳደርና የሒሳብ አሰራር ስርአት እና ሪፖርት አቀራረብ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን አቶ ዘበነ ገዛኸኝ ከፌደራል የመንግስት ግዥ እና ንብረት ባለስልጣን ፣ አቶ ደበበ ማሞ ከመንግስት ግዥ አስተዳደር እና አቶ አማረ ደረሰ ከገንዘብ ሚኒስቴር ስልጠናውን ሰጥተዋል፡፡የተቀናጀ ተቋማዊ ሙስናን መከላከል ሰትራቴጂ አፈጻጸም፣ የመንግስት ተቋማት ሙስናን የመከላከል ኃላፊነት፤ በተቋማት ሙስናና ብልሹ አሰራርን በተቀናጀ ሁኔታ የመከላከል አንጻራዊ ጠቀሜታዎች እና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጰያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ዳይሬክተር አቶ ልኡልሰገድ አበበ የመወያያ ሰነድ አቅርበዋል፡፡የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሙሉጌታ እና ወ/ሮ መቅደስ ስራብዙ የፋይናንስ ግልጽነት እና ተጠያቂነት መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን በየማዕከላቱ ያጋጠሙ የኦዲት ግኝቶችን ለሌሎች አስተማሪ በሆነ መልኩ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እንድሪስ ሀሰን በመሰረታዊ የሲቪል ሰርቪስ ህጎች፣ የሰው ሀብት ስራ አመራር ተግባራት እና ከሰው ሀብት አስተዳደር ጋር ተያይዞ አዋጆች ደንቦች እና መመሪያዎች ምን እንደሚሉ አብራርተዋል። የሴቶች፣ሕጻናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ከበደ ስለ ስርአተ ጾታና የህግ ማእቀፎች፣የስርአተ ጾታ ምንነት፣ስርዓተ ጾታን ማካተት፣የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት መጨመር፣ የስርአተ ጾታ እኩልነት፣የሴቶች ጉዳይ ላይ መሰረት የሆኑ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ስምምነቶች፣ፖሊሲዎች ፣ህጎች እና የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ የሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰነድ አቅርበዋል። የኢንስቲትዩቱን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓቶችን ከማስተዋወቅ አንጻር የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ወርቁ የኢንስቲትዩቱ ድረ-ገጽ፣ ኢንትራኔት፣ ፎቶ ጋለሪ፣ ኢ-ላይብረሪ እና ጂኦ-ፖርታል የተሰኙ በክፍሉ በኩል ለምተው ግልጋሎት እየሰጡ የሚገኙ ሲስተሞች ዙሪያ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሲስተሞቹ ለመረጃ ፈላጊዎች መረጃዎችን በመስጠት የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱን የተሳለጠ እንዲሆን በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ መድረኩን በዘጉበት ወቅት “እንደ አጠቃላይ ከዋና መስሪያ ቤት እስከ ማዕከላት ያለው አዲስ አደረጃጀት በመሆኑ ስልጠናው የተሰጠበት አግባብ ወቅቱን የጠበቀ ሲሆን፣ የተነሱት ጉዳዮችም እጅግ በጣም ጠቃሚ እና አስፈላጊ ናቸው” ብለዋል።