በማህበረሰብ ዘር ባንክ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በምስራቅ ወለጋ ዞን ተካሄደ
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በምስራቅ ወለጋ ዞን ለካ ዱለቻ የማህበረሰብ ዘር ባንክ አባላት ተሰጥቷል።
በስልጠናው ላይ በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የማሳ ላይ ማንበር እና የማህበራዊ ዘር ባንክ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ውብሸት ተሾመ ለካ ዱለቻ አካባቢ የሚመረቱ የተለያዩ ዓይነት የሰብል ዓይነቶች ሊጠፉ መቃረባቸውን አስታውሰው የአገር በቀል ዝርያዎችን መልሶ ለመተካት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዝርያዎቹ ላይ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ዝርያዎቹ ከማዕከላዊ ጂን ባንክ በማውጣት እንዲያመርቱ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰጡ አቶ ውብሸት ጠቅሰዋል።
ይህም የጠፉ ዝርያዎችን ለመተካት እና በዘላቂነት ለመጠቀም ያገለግላል ብለዋል።
የለካ ዱለቻ ማህበረሰብ ዘር ባንክ ሊቀመንበር አቶ ቦሬ ጨዋቃ በበኩላቸው ነባሮቹ ዝርያዎች አካባቢውን በደንብ የተላመዱና የተመረጡ በመሆናቸው ሲተከሉ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
ስለሆነም የተለያዩ ዝርያዎች እንዲዳረሱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች የዘር ባንክ አባል የመሆን ፍላጎታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ሊቀመንበሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በ 2008 የተቋቋመው የለካ ዱለቻ ማህበረሰብ ዘር ባንክ አሁን 66 አባላት ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 21 ቱ ሴቶች ናቸው።
ሥልጠናው አባላቱ በባለቤትነት ስሜት በንቃት እንዲሳተፉ ለማነሳሳት የተነደፈ ነው።
በሀገሪቱ 23 የማህበረሰብ ዘር ባንኮች ተቋቁመዋል።